ከደን_ምርምር_ስራዎች_መካከል
የቀርከሃ_ዝርያዎችን_ማላመድ_የማራባት_እና_የማባዛት_ሥራዎች
አማራ ክልል በቀርከሃ ከፍተኛ የመልማት አቅም ያለው በመሆኑ የተለያዩ የቀርከሃ ዝርያዎችን ከተለያዩ አካባቢዎች በማስገባት የማላመድና የአረባብ ዘዴ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ስለዚህም ፈጣን ዕድገት ያለውና ከፍተኛ ባዮማስ የሚሰጠውን የግዙፍ ቀርከሃን የዕድገት ሆርሞኖችን (አይ.ቢ.ኤ እና ጂ.ኤ3) በመጠቀም ከግንዱ (culm) የተለያዩ ክፍሎች (ከታች፣ ከመሃል እና ከጫፍ) ቁርጥራጭ በመውሰድ ማባዛት ተችሏል፡፡ በተለይም ከመሃል የተወሰደው የግንድ ቁርጥራጭ የዕድገት ሆርሞኖችን በመጠቀም ከ60% በላይ መጽደቅ የሚችል መሆኑ ታይቷል፡፡
የዕድገት ሁኔታው ሲገመገም በሦስት ዓመት ተኩል በአማካይ 9.5 ሜ ቁመት፣ 6.7 ሳ.ሜ. ውፍረት እና 29 አዳዲስ አጣናዎች (culms) ማውጣት ችሏል፡፡ በሃርቡ ወረዳ ችግኝ ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው የግዙፍ ቀርከሃ እንደሚያሳየው ዕድሜው እየጨመረ ሲመጣ እስከ 228 አጣናዎች፣ እስከ 20 ሜትር ቁመት እና እስከ 25 ሳ.ሜ. ውፍረት ያድጋል፡፡ ለምሳሌ የደጋ ቀርከሃ እስከ 48000 አጣናዎች በሄ/ር፣ ውፍረት ከ0.3 – 10.5 ሳሜ እና ቁመት ከ2.1 - 20.6 ሜ ማደግ ይችላል፡፡ ግዙፍ ቀርከሃ ከደጋ ቀርከሃ ጋር ሲወዳደር በውፍረት እስከ ሶስት ጊዜ እጥፍ እና በቁመት በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ ያሳያል፡፡ በተመሳሳይ የቆላ ቀርከሃ እስከ 185400 ሽመል (አጣናዎች) በሄ/ር፣ ውፍረት ከ2.6 – 3 ሳሜ እና ቁመት ከ6.1 – 9.3 ሜ ማደግ ይችላል፡፡ ስለዚህም ግዙፍ ቀርከሃ ከሽመል ጋር ሲነጻጸር በውፍረት እስከ 8 ጊዜ እጥፍ እና በቁመት በሶስት እጥፍ እና በላይ እንደሚበልጥ ያሳያል፡፡ ግዙፍ ቀርከሃ ብዙ አጣናዎችን ማውጣት ስለሚችል የተከላ ርቀቱ 8ሜ በ8ሜ ያላነሰ ቢሆን ይመከራል፡፡
በቆላማው የቆቦ አካባቢ ባመቡሳ ቱሉዳ እና ባልካዖ የተባሉ የቀርከሃ ዝርያዎችን በማላመድ ለዝናብ አጠር አካባቢዎች 2ሜ በ2ሜ የተከላ ርቀት ተተክለው ተገምግመዋል፡፡ በፅድቀት መጠን ሲገመገሙ ባልካዖ 100% እና ባምቡሳ ቱሉዳ 94.4% ነበር፡፡ 2 m X 2 m ባምቡሳ ቱሉዳ 3.8 ሳሜ ውፍረት እና 6.3 ሜ ቁመት፣ ባምቡሳ ባልካዖ 2.9 ሳሜ ውፍረት እና 5.6 ሜ ቁመት እንዲሁም ዴንድሮካልመስ አስፐር 2.8 ሳሜ ውፍረት እና 5.0 ሜ ቁመት በአምስት ዓመት ተኩል ማደግ ችለዋል፡፡ ባልካዖ 22 አጣናዎችን በማውጣት የተሻለ ነበር፡፡ ስለሆነም እነዚህ ቀርከሃዎች በአካባቢው አዲስ በመሆናቸው ለቀርከሃ ምርት፣ ለአፈርና ውሃ ጥበቃና ለመኖ እንዲተከሉ ተመክረዋል፡፡
በጣርማበር ወረዳ (አርመኒያ) ቀበሌ እና በኤፍራታና ግድም (አጣዬ) አራት የቀርከሃ ዝርያዎች (ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ፣ ዴንድሮካልመስ ሀሚልቶኒ፣ ባምቡሳ ቩልጋሪስ እና የቆላ ቀርቀሃ (ሽመል) ተላምደዋል፡፡ አጣዬ አካባቢ ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ 2.2 ሜ ቁመት፣ 1.1 ሳ.ሜ ውፍረት እና በአማካይ 5.7 አዳዲስ ፍንጭቶች በአንድ ዓመት አውጥቷል፡፡
የቆላ ቀርቀሃ 2.2 ሜ፣ 1.3 ሳ.ሜ ውፍረት በአማካይ 5.4 አዳዲስ ፍንጭቶች አውጥቷል፡፡ ዴንድሮ ካልመስ ሀሚልቶኒ ቁመት 3.5 ሜ፣ 2.7 ሳ.ሜ ውፍረት እና 4.5 አዳዲስ ፍንጭቶች አውጥቷል፡፡ ለአርሶ አደር ከተሰራጩት ውስጥ የቆላ ቀርቀሃ 1.8 ሜ እና 1.3 ሳ.ሜ ውፍረት በማደግ የተሻለ ሆኗል፡፡ ሦስት የቀርከሃ ዓይነቶችን (ዴንድሮካልመስ ሀሚልቶኒ፣ ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ እና ባምቡሳ ሜምብራሼስ) ለአርመንያና አጣዬ አካባቢዎች የተላመዱ በመሆኑ በተመሳሳይ ስነምህዳሮች አንዲተከሉ ተመከርዋል፡፡ በወይና ደጋ አካባቢ ዴንድሮካልመስ ሀሚልቶኒ፣ ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ እና ባምቡሳ ሜምብራሼስ ተላምደው እንዲተከሉ ተመክረዋል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ የቀርከሃ ዝርያዎች የተሻሉ ምርታማ ከመሆናቸው በተጨማሪ በተለያዩ ስነምህዳሮች መብቀል የሚችሉ በመሆኑ የክልሉን የቀርከሃ ብዝሃ-ሕይወት ስብጥር የሚያሻሽሉ እና ለቀርከሃ ልማት አማራጭ የቀርከሃ ዓይነቶች ናቸው፡፡

