News

Print PDF

የምግብና ምርታማነት ማሻሻያ ፕሮጀክት (Inno Food Project) ያከናወናቸውን ስራዎች የተመለከተ ግምገማዊ አውደ ጥናት አካሄደ::

የምግብና ምርታማነት ማሻሻያ ፕሮጀክት በአማራ ክልል በተመረጡ ቦታዎች ምርታማነትን የሚያሻሽሉ አሳታፊ የዝርያ መረጣ ስራዎችን፣ የምርት ብክነትን ለማስቀረት የሚያስችሉ አሰራሮችን፣ ከግብርና እሴት ሰንሰለት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ያለሙ እንዲሁም በዘር ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የምርምር ስራዎችን በመስራት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ አልሞ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአንድ አመት ውስጥ ያከናወናቸው የምርምር ስራዎች ያሉበትን ደረጃ የሚገመግም አውደ ጥናት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል፡፡

በአውደ ጥናቱ የተገኙት የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላዬ ተክለወልድ በፕሮጀክቱ በኩል የአርሶ አደሩን ችግር የሚፈቱ አሰራሮችን ማሻሻል፣ ማስተዋወቅና የሚጎድሉ ስራዎችን እየገመገምን ማስተካከል ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የያዛቸው ግቦች እንዲሳኩ ተመራማሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም ዶ/ር ጥላዬ አሳስበዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዋጋ ማዘንጊያ የፕሮጀክቱን አላማና እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎችን ለአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ያቀረቡ ሲሆን ፕሮጀክቱ በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ ያለውን ዝቅተኛ ምርታማነት ለማሻሻል፣ በከተማና አለም አቀፍ ገቢያዎች ያለውን የግብርና ምርቶች የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ አልሞ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ በጤፍ፣ በበቆሎ፣ ባቄላ እና ስኳር ድንች ሰብሎች ላይ የተሰሩ ማህበረሰቡን ያሳተፉ የዝርያ መረጣ የጥናት ውጤቶች፣ ከእሴት ሰንሰለትና ከምርት ብክነት እንዲሁም ከዘር ስርዓቱ ጋር የተያያዙ የምርምር ስራዎች በተመራማሪዎች ቀርበው ግምገማ ተደርጎባቸዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም ፕሮጀክቱ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ተግባሩን እንዲፈጽም ተቀናጅተው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

Inno Food Project በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳና በአዊ ዞን ባንጃ ወረዳ ትኩረት አድርጎ ተግባሩን እያከናወነ የሚገኝ አለም አቀፍ ፕሮጀክት ነው፡፡

Last Updated ( Monday, 04 April 2022 12:31 )
 
Print PDF

በሲሪንቃ እና ሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከላት ላይ የደረሰው ውድመትThe damage on Sirinka and Sekota Research Centers

በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኘው የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከልና በዋግኸምራ ዞን የሚገኘው የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል ከህወሃት ጋር በተደረገው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ምርምር ማዕከላቱ አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገው ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡ በዚህ ቪዲዮ በተቋማቱ ላይ የደረሰውን አስከፊ ውድመት ትመለከታላችሁ፡

ቪዲዮውን ይመልከቱ!

Last Updated ( Friday, 01 April 2022 13:13 )
 
Print PDF

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት CultiviAid ከተሰኘ የእሰራኤል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር የክልሉን ግብርና ለማዘመንና በትብብር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላዬ ተክለወልድ እና የ CultiviAid ተወካይ ቶመር ማልች ተፈራርመዋል፡፡ በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት እስራኤል በግብርናው ዘርፍ ያላትን እውቀትና ቴክኖሎጅ ለአማራ ክልል ለማጋራትና ሽግግር እንዲኖር ለማስቻል ሁለቱ ተቋማት በትብብር ይሰራሉ፡፡ የትብብር ስምምነቱ በተመረጡ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመነሻነት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

በዚህም በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ በወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ምርምርና ስልጠና ንዑስ ማዕከል፣ በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን፣ በሰሜን ወሎ በቆቦ ጊራና፣  በሰቆጣ ቃልኪዳን ልዩ ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ዝናብ አጠር አካባቢዎችና በመገጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ምርምር ኢንስቲትዩቱ በሚያከናውናቸው የምርምር እና ስልጠና ተግባራት ውስጥ ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎች በትብብር ይሰራሉ፡፡ በተለይም የእውቀት ሽግግር እንዲኖርና የምርምር ማዕከላትን የመፈጸም አቅም ለማጠናከር የትብብር ስምምነቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ዶ/ር ጥላዬ እንዳሉት እስራኤል በግብርናው ዘርፍ ያላትን የዳበረ ተሞክሮ ወደ አማራ ክልል በማምጣት የእውቀትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ ከCultiviAid ጋር በትብብር መስራቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአፈርና ውሃ አያያዝ፣ በእሴት ሰንሰለት እና በገበያ ትስስር በኩል ያሉ ልምዶችን ወደ ክልሉ ለማምጣት CultiviAid ጉልህ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት አለን ብለዋል፡፡

የCultiviAid ተወካይ ቶመር ማልች በበኩላቸው እስራኤል በግብርናው ዘርፍ ያላትን ከፍተኛ ልምድ ለማካፈልና ከአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ለመስራት በመስማማታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው በአማራ ክልል በዘርፉ ያለውን የእውቀት ክፍተት ለመሙላት ተቋማቸው በሚችለው አቅም ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓት የምርምር ኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤርሚያስ አባተ እና የኢንሰቲትዩቱ ቴክኒካል ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል፡፡ CultiviAid እስራኤል ውስጥ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያ በግብርና እና ውሃ ሴክተሮች በአቅም ግንባታ፣ እውቀትና ቴክኖሎጅ ሽግግር ዘርፎች ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡

c123

c1234

c12345

Last Updated ( Friday, 30 July 2021 13:41 )
 
Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

ከደን_ምርምር_ስራዎች_መካከል

የቀርከሃ_ዝርያዎችን_ማላመድ_የማራባት_እና_የማባዛት_ሥራዎች

አማራ ክልል በቀርከሃ ከፍተኛ የመልማት አቅም ያለው በመሆኑ የተለያዩ የቀርከሃ ዝርያዎችን ከተለያዩ አካባቢዎች በማስገባት የማላመድና የአረባብ ዘዴ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ስለዚህም ፈጣን ዕድገት ያለውና ከፍተኛ ባዮማስ የሚሰጠውን የግዙፍ ቀርከሃን የዕድገት ሆርሞኖችን (አይ.ቢ.ኤ እና ጂ.ኤ3) በመጠቀም ከግንዱ (culm) የተለያዩ ክፍሎች (ከታች፣ ከመሃል እና ከጫፍ) ቁርጥራጭ በመውሰድ ማባዛት ተችሏል፡፡ በተለይም ከመሃል የተወሰደው የግንድ ቁርጥራጭ የዕድገት ሆርሞኖችን በመጠቀም ከ60% በላይ መጽደቅ የሚችል መሆኑ ታይቷል፡፡

የዕድገት ሁኔታው ሲገመገም በሦስት ዓመት ተኩል በአማካይ 9.5 ሜ ቁመት፣ 6.7 ሳ.ሜ. ውፍረት እና 29 አዳዲስ አጣናዎች (culms) ማውጣት ችሏል፡፡ በሃርቡ ወረዳ ችግኝ ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው የግዙፍ ቀርከሃ እንደሚያሳየው ዕድሜው እየጨመረ ሲመጣ እስከ 228 አጣናዎች፣ እስከ 20 ሜትር ቁመት እና እስከ 25 ሳ.ሜ. ውፍረት ያድጋል፡፡  ለምሳሌ የደጋ ቀርከሃ እስከ 48000 አጣናዎች በሄ/ር፣ ውፍረት ከ0.3 – 10.5 ሳሜ እና ቁመት ከ2.1 - 20.6 ሜ ማደግ ይችላል፡፡ ግዙፍ ቀርከሃ ከደጋ ቀርከሃ ጋር ሲወዳደር በውፍረት እስከ ሶስት ጊዜ እጥፍ እና በቁመት በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ ያሳያል፡፡ በተመሳሳይ የቆላ ቀርከሃ እስከ 185400 ሽመል (አጣናዎች) በሄ/ር፣ ውፍረት ከ2.6 – 3 ሳሜ እና ቁመት ከ6.1 – 9.3 ሜ ማደግ ይችላል፡፡ ስለዚህም ግዙፍ ቀርከሃ ከሽመል ጋር ሲነጻጸር በውፍረት እስከ 8 ጊዜ እጥፍ እና በቁመት በሶስት እጥፍ እና በላይ እንደሚበልጥ ያሳያል፡፡ ግዙፍ ቀርከሃ ብዙ አጣናዎችን ማውጣት ስለሚችል የተከላ ርቀቱ 8ሜ በ8ሜ ያላነሰ ቢሆን ይመከራል፡፡

በቆላማው የቆቦ አካባቢ ባመቡሳ ቱሉዳ እና ባልካዖ የተባሉ የቀርከሃ ዝርያዎችን በማላመድ ለዝናብ አጠር አካባቢዎች 2ሜ በ2ሜ የተከላ ርቀት ተተክለው ተገምግመዋል፡፡ በፅድቀት መጠን ሲገመገሙ ባልካዖ 100% እና ባምቡሳ ቱሉዳ 94.4% ነበር፡፡ 2 m X 2 m ባምቡሳ ቱሉዳ  3.8 ሳሜ ውፍረት እና 6.3 ሜ ቁመት፣ ባምቡሳ ባልካዖ 2.9 ሳሜ ውፍረት እና 5.6 ሜ ቁመት እንዲሁም ዴንድሮካልመስ አስፐር 2.8 ሳሜ ውፍረት እና 5.0 ሜ ቁመት በአምስት ዓመት ተኩል ማደግ ችለዋል፡፡ ባልካዖ 22 አጣናዎችን  በማውጣት የተሻለ ነበር፡፡ ስለሆነም እነዚህ ቀርከሃዎች በአካባቢው አዲስ በመሆናቸው ለቀርከሃ ምርት፣ ለአፈርና ውሃ ጥበቃና ለመኖ እንዲተከሉ ተመክረዋል፡፡

በጣርማበር ወረዳ (አርመኒያ) ቀበሌ እና በኤፍራታና ግድም (አጣዬ) አራት የቀርከሃ ዝርያዎች  (ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ፣ ዴንድሮካልመስ ሀሚልቶኒ፣ ባምቡሳ ቩልጋሪስ እና የቆላ ቀርቀሃ (ሽመል) ተላምደዋል፡፡ አጣዬ አካባቢ ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ 2.2 ሜ ቁመት፣ 1.1 ሳ.ሜ ውፍረት እና በአማካይ 5.7 አዳዲስ ፍንጭቶች በአንድ ዓመት አውጥቷል፡፡

የቆላ ቀርቀሃ 2.2 ሜ፣ 1.3 ሳ.ሜ ውፍረት በአማካይ 5.4 አዳዲስ ፍንጭቶች አውጥቷል፡፡ ዴንድሮ ካልመስ ሀሚልቶኒ ቁመት 3.5 ሜ፣ 2.7 ሳ.ሜ ውፍረት እና 4.5  አዳዲስ ፍንጭቶች አውጥቷል፡፡ ለአርሶ አደር ከተሰራጩት ውስጥ የቆላ ቀርቀሃ 1.8 ሜ እና 1.3 ሳ.ሜ ውፍረት በማደግ የተሻለ ሆኗል፡፡ ሦስት የቀርከሃ ዓይነቶችን (ዴንድሮካልመስ ሀሚልቶኒ፣ ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ እና ባምቡሳ ሜምብራሼስ)  ለአርመንያና አጣዬ አካባቢዎች የተላመዱ በመሆኑ በተመሳሳይ ስነምህዳሮች አንዲተከሉ ተመከርዋል፡፡ በወይና ደጋ አካባቢ ዴንድሮካልመስ ሀሚልቶኒ፣ ጉዱዋ አምፕሊክስፎሊያ እና ባምቡሳ ሜምብራሼስ ተላምደው እንዲተከሉ ተመክረዋል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ የቀርከሃ ዝርያዎች የተሻሉ ምርታማ ከመሆናቸው በተጨማሪ በተለያዩ ስነምህዳሮች መብቀል የሚችሉ በመሆኑ የክልሉን የቀርከሃ ብዝሃ-ሕይወት ስብጥር የሚያሻሽሉ እና ለቀርከሃ ልማት አማራጭ የቀርከሃ ዓይነቶች ናቸው፡፡

ff23

 

Last Updated ( Friday, 30 July 2021 13:43 )
 
Print PDF

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በክልሉ ግብርና ቢሮ የተገዙ 2 የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች ተረከበ፡፡

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላዬ ተክለወልድ እንደገለጹት ምርምር ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው መነሻ ዘር ሰብስቦ ለዘር አባዥ ተቋማት ለማድረስ ከዚህ በፊት የምርት መሰብሰቢያ ማሽን ችግር ስለነበረበት የመነሻ ዘር የሚታጨደውና የሚወቃው በባህላዊ መንገድ በመሆኑ ጥራት ያለውና ከብክነት ነጻ የሆነ ምርት ለመሰብሰብ እንቅፋት ሆኖበት ቆይቷል፡፡ ይህን ችግር የተረዳው የክልሉ ግብርና ቢሮ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው 2 ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች ገዝቶ ሰጥቶናል ብለዋል፡፡ኮምባይነሮቹ በምርት ስብሰባ ወቅት የሚፈጠር የምርት ብክነት ለመቀነስና ጥራት ያለው የመነሻ ዘር ለማምረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ዶ/ር ጥላዬ ተናግረዋል፡፡ በምርምር ማዕከላት የሚመረቱ መነሻ ዘሮችን ከመሰብሰብ ባለፈ ማዕከላቱ በሚገኙበት አካባቢ ለሚኖረው ማህበረሰብም አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው የማሽኖቹ ጥቅም ዘርፈ ብዙ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ኮባይነሮቹን ገዝቶ ለኢንስቲትዩቱ የሰጠው የክልሉ ግብርና ቢሮ ሲሆን ቢሮው ልዩ ትኩረት በማድረግ ምርምር ኢንስቲትዩቱ በዘመናዊ ማሽኖች እንዲጠናከር እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ዶ/ር ጥላዬ በኢንስቲትዩቱ ስም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

20312030

Last Updated ( Monday, 19 July 2021 09:12 )
 
 • «
 •  Start 
 •  Prev 
 •  1 
 •  2 
 •  3 
 •  4 
 •  5 
 •  6 
 •  7 
 •  8 
 •  9 
 •  10 
 •  Next 
 •  End 
 • »
Page 1 of 28
You are here: Home News