Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

የምርምር_ምክረ_ሀሳቦች

#የናይትሮጅን_የፎስፈረስ_የፖታሲዬም_እና_የሰልፈር_ንጥረ_ነገሮች_አስፈላጊነት_ጥናት_ውጤት

#ለጤፍ_ሰብል

 #ናይትሮጂን፣ ለጤፍ ሰብል በጃማ በሄክታር 69 ኪ.ግ. ናይትሮጂንና 46 ኪ.ግ. ፎስፈረስ (P2O5) መጨመር ማዳበሪያ ካልተጨመረበት ጋር ሲወዳደር የ5 ኩ/ል የምርት ብልጫ ያሳየ ሲሆን ከዚህ በላይ መጨመር ጉልህ የሆነ የምርት ጭማሪ እንደማያስገኝ የጥናቱ ውጤት ያሳያል፡፡ የፖታሺየም እና ሰልፈር ንጥረ ነገሮች ለአካባቢው ከተመከረው ማዳበሪያ መጠን የተሻለ የምርት ጭማሪ አላስገኙም፡፡

 #በደልጊ ለጤፍ #በፖታሺየምና #በሰልፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ ተጠኚዎች መካከል የምርት ልዩነት ያልታየ ሲሆን በናይትሮጂንና በፎሰፎረስ ተጠኚዎች መካከል ግን ልዩነት ታይቷል፡፡ በመሆኑም 69 ኪ/ግ ናይትሮጂን በሄ/ር ለጤፍ መጨመር 17.24 ኩ/ል በሄ/ር ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ያለው ምርት አስገኝቷል፡፡ ይህም ሌሎች ንጥረ ነገሮች ተጨምረው ናይትሮጂን ብቻ ካልተጨመረበት ተጠኝ የ7.6 ኩ/ል ወይም 78.8% ምርት ብልጫ ሲያስገኝ፣ 161 ኪ.ግ. ናይትሮጂንና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ከተጨመሩበት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የጎላ ምርት ልዩነት አላሳየም፡፡ በተመሳሳይ 46 ኪ/ግ ፎስፎረስ (P2O5) በሄ/ር ለጤፍ መጨመር 16.6 ኩ/ል የጤፍ ምርት በሄ/ር ያስገኘ ሲሆን ይህም ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ያለው ምርት ነው፡፡ ይህም ሁሉም ንጥረ ነገሮች ተጨምረው ፎስፈረስ ብቻ ካልተጨመረበት ተጠኚ የ10% ምርት ጭማሪ ሲያስገኝ 115 ኪ.ግ ፎስፈረስ (P2O5) ከተጨመረበት ተጠኝ ግን የጎላ የምርት ልዩነት የለውም፡፡ በመሆኑም ለጤፍ ምርት ጭማሪ ናይትሮጂንና ፎስፈረስ (P2O5) ንጥረ ነገሮች አስፈላጊ መሆናቸውን ፖታሲየምና ሰልፈር ለጊዜው እንደማያስፈልጉ ተረጋግጧል፡፡

 #በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለቡናማ አፈርና ለጥቁር አፈር ዓይነቶች ኢኮኖሚያዊ አዋጪ እና የተሻለ የጤፍ ምርት (18 ኩ/ል በሄ/ር) ያስገኘው የ46 ኪ.ግ. #ናይትሮጂንና የ46 ኪ.ግ. #ፎስፎረስ (P2O5) ጥምረት ነው፡፡ ይህም ምንም ካልተጨመረበት ማሳ በሄ/ር ከተገኘው ስምንት ኩ/ል ምርት ጋር ሲነጻጸር የ10 ኩ/ል ወይም የ125% ምርት ብልጫ አለው፡፡ በመሆኑም ለጎንደር ዙሪያና ተመሳሳይ ቡናማና ጥቁር አፈር አካባቢዎች 46 ኪ.ግ. ናይትሮጂንና 46 ኪ.ግ ፎስፈረስ (P2O5) መጠቀም ይመከራል፡፡

 

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2013ዓ.ም 7 አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን አስለቀቀ

 

ምርምር ኢንስቲትዩቱ በስሩ በሚገኙ የምርምር ማዕከላት አማካኝነት 7 የሰብል ዝርያዎችን ማስለቀቁን በኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ አሰፋ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አዲስ የብቅል ገብስ ዝርያ ያስለቀቀ ሲሆን ዝርያው በሀገሪቱ ካሉት የብቅል ገብስ አይነቶች የተሻለ ጥራት ያለውና ምርታማ ነው፡፡ ዝርያው ቢራ ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ማሟላቱ የተረጋገጠ ሲሆን ከዚህ በፊት ከነበሩት ባለ ሁለት ጠርዝ የብቅል ገብስ ዝርያዎች በተለየ 6 ጠርዝ ያለው ነው፡፡ አሁን ላይ በአማራ ክልል አርሶ አደሮች ከሚያመርቱት IBON-174/03 ከተሰኘው ዝርያ ጋር ሲነጻጸርም የ13.6 በመቶ የምርት ጭማሪ አለው፡፡ ይህም በአማካኝ እስከ 50 ኩንታል በሄክታር ምርት መስጠት የሚችል ሲሆን የብቅል ገብስን የሚያጠቁ በሽታዎችን የመቋቋም አቅሙም ከፍተኛ ነው፡፡

ሌላው በደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል አዲስ የባቄላ ዝርያ ተለቋል፡፡ ዝርያው ከዚህ በፊት በምርታማነታቸው ከሚታወቁ ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸር ተቀራራቢ ምርት የሚሰጥ ሲሆን ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ትልልቅ ፍሬ ያለው በመሆኑ የውጭ ገበያን ትኩረት የሚስብ፣ በደጋማ አካባቢዎች በስፋት መመረት የሚችልና በሽታ የመቋቋም አቅሙም በአንጻራዊነት የተሻለ የሆነ ዝርያ ነው፡፡ ይህ ዝርያ ጥቁር አፈር ባላቸው አካባቢዎችና በደጋማ ቦታዎች የሚመረት መሆኑ የተሻለ ያደርገዋል፡፡ ዝርያው በአማካኝ እስከ 39 ኩንታል ምርት በሄክታር የመስጠት አቅም አለው፡፡ ኢንስቲትዩቱ አዲስ የባቄላ ዝርያ ሲያስለቅቅ ከ1997ዓ.ም ወዲህ የመጀመሪያው ነው፡፡

በ2013ዓ.ም የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል አዲስ የጤፍ ዝርያ ያስለቀቀ ሲሆን ዝርያው ከአሁን በፊት አርሶ አደሩ ከሚጠቀመው “አባይ” የተሰኘ የጤፍ ዝርያ ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ የምርት ጭማሪ ያለው ሲሆን ጣቁሳ አካባቢ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ከሚገኘው “ጸደይ” የተሰኘ ዝርያ ደግሞ የ31.3 በመቶ የምርት ጭማሪ አለው፡፡ ዝርያው ነጭ ቀለም ያለው እና ፈጥኖ የሚደርስ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ በተለይም ቀድሞ የሚደርስ መሆኑ ጥቁር አፈር ባላቸውና እርጥበትን ይዘው በሚቆዩ አካባቢዎች የጤፉ ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ ሌሎች ሰብሎችን ለመዝራት እድል የሚፈጥር ነው፡፡

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አዲስ የሽንብራ ዝርያም አስለቅቋል፡፡ ዝርያው በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውለው “ዲምጡ” ከተሰኘው ዝርያ ጋር ሲነጻጸር የ28.18 በመቶ የምርት ጭማሪ ያለው ወይም 21.12 ኩንታል ምርት በሄክታር መስጠት የሚችል ነው፡፡ ዝርያው ቀይ ቀለም ያለው፣ ሽንብራን የሚያጠቁ በሽታዎችን በአንጻራዊነት መቋቋም የሚችል፣ በገበያ ተፈላጊ እና ወደ ውጭ የሚላኩ የሽንብራ ምርቶችን ደረጃ ያሟላ ዝርያ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ደግሞ አዲስ የቦሎቄ ዝርያ አስለቅቋል፡፡ ዝርያው 27.29 ኩ/ል በሄክታር መስጠት የሚችልና የተሻለ ምርት አለው ተብሎ ከሚታሰበው “አዋሽ 2” ከተሰኘው ዝርያ የ23.6 በመቶ የምርት ጭማሪ ያለው ነው፡፡ በሽታና ድርቅ የመቋቋም አቅሙ የተሻለ በመሆኑ ተመራጭ ሊሆን የሚችል ዝርያ ነው፡፡

አዲስ የአተር ዝርያም በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ተለቋል፡፡ ዝርያው ከዚህ በፊት ከሚታወቀው “ተሻለ” ከተሰኘው የአተር ዝርያ ጋር ሲነጻጸር የ21.76 በመቶ የምርት ብልጫ ያለውና በአማካኝ 23.17 ኩ/ል ምርት በሄክታር የሚሰጥ ነው፡፡ ነጭ ቀለም ያለው፣ በአርሶ አደሮች ግምገማ ተመራጭ ዝርያ መሆኑና ከምስር ጋር እኩል ጠቀሜታ ያለው ሊሆን እንደሚችልም አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች በኩል የደብረ-ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል እጅግ ምርታማ የሆነ አዲስ የነጭ ሽንኩርት ዝርያ አስለቅቋል፡፡ ዝርያው ከአካባቢው የሽንኩርት ዝርያ የ40% የምርት ጭማሪ ያለው ወይም 130.3 ኩንታል ምርት በሄክታር መስጠት የሚችል ነው፡፡ ዝርያው ትልልቅ መጠን ያለው፣ ሙሉ ነጭ የሆነ፣ በሽታ የመቋቋም አቅሙ የተሻለ እና በከፍተኛ ቦታዎች አካባቢ መላመድ የሚችል ዝርያ ነው፡፡ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አዲስ የነጭ ሽንኩርት ዝርያ ሲያስለቅቅ የመጀመሪያው መሆኑንም ዶ/ር አለማየሁ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ዝርያዎቹ ወደ አርሶ አደሩ ወርደው የተሻለ ጥቅም እንዲሰጡ የአራቢ ዘር የማባዛት፣ የማስተዋወቅና የቅድመ-ማስፋት ስራዎች በስፋት እንደሚሰሩ ዶ/ር አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

ce123

 

Last Updated ( Thursday, 24 June 2021 13:47 )  
You are here: Home News News የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በ2013ዓ.ም 7 አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን አስለቀቀ