Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

የሙዝ ሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ምርምርና ስልጠና ንዑስ ማዕከል አስታወቀ

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኘው የወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ምርምርና ስልጠና ንዑስ ማዕከል በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡ ንዑስ ማዕከሉ በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች ሙዝን በዘመናዊ መንገድ አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ ሲሆን በፕሮጀክቱ ውስጥ ተጠቃሚ በሆኑ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የመስክ ቀን ተካሂዷል፡፡

በመስክ ቀኑ በወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ምርምርና ስልጠና ንዑስ የአትክልትና ፍራፍሬ ተመራማሪ አቶ ምንውየለት ጀምበሬ ንዑስ ማዕከሉ አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን በስፋት አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን መንደርን መሰረት ያደረገ የሙዝ ልማት ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም በክልሉ በ11 ወረዳዎች የሙዝ መንደርን በመመስረት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና ያለውን የገበያ ፍላጎት ለመሙላት እየተሰራ ነው ያሉት ተመራማሪው 4 ምርታማ ዝርያዎችን (ፓዮ፣ ግራንድካቫዲሽ፣ ቡታዞ እና ዊሊያምስ 1 የተሰኙ) የማስተዋወቅና ስራውን የበለጠ የማስፋት ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ዝርያዎቹ ከአካባቢው ዝርያ ጋር ሲነጻጸሩ ትልልቅ መጠን ያለው የሙዝ ምርት የሚሰጡ፣ የተሻለ ጣዕም ያላቸውና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ፣ በአንድ የሙዝ ዛፍ ላይ ከነባሩ ዝርያ በተሻለ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና ጠንካራ ቆዳ ያላቸው በመሆኑ ቶሎ የማይበላሹ ናቸው፡፡

በቆጋ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ውስጥ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን እያለሙ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አበጀ አስማረ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ነባሩን የአካባቢ ሙዝ ዝርያ ያለሙ እንደነበር ገልጸው በንዑስ ምርምር ማዕከሉ የቀረቡላቸው የተሻሻሉት ዝርያዎች በፊት ከነበረው የአካባቢ ዝርያ በተሻለ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በምርምር ተቋሙ የቀረቡት ዝርያዎች በቀላሉ የማይበላሹ፣ ምርታማ እና በገበያ ተፈላጊ መሆናቸውን የጠቀሱት አርሶ አደሩ ስራው በአግባቡ ከተያዘ ተጠቃሚ ስለሚያደርገን በቀጣይም በስፋት እንገባበታለን ብለዋል፡፡

እስካሁን ነባሩን የሙዝ ዝርያ ብቻ እያለሙ የሚገኙና በመስክ ቀኑ የተገኙት ሌላኛው አርሶ አደር ይመር ምስክር አዲሱን የሙዝ ዝርያ ተጠቃሚ ላያደርገኝ ይችላል በሚል ተጠራጥሬው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ብዙ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ስለተረዳሁ በቀጣይ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን ለማልማት ዝግጁ ነኝ በማለት ተናግረዋል፡፡

የወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ምርምርና ስልጠና ንዑስ ማዕከል በክልሉ ብቸኛው የአትክልትና ፍራፍሬ የምርምር እና ስልጠና ን/ማዕከል ሲሆን በቀጣይ ወደ ማዕከልነት በማደግ በዘርፉ ክልሉን የበለጠ ይጠቅማል ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ን/ማዕከል ነው፡፡

b373

 

b273

 

Last Updated ( Thursday, 24 June 2021 13:57 )  
You are here: Home News News የሙዝ ሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ