የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ለቆላማ አካባቢዎች የሚስማማ የቀቀባ ስንዴ ዝርያ መረጣ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
በደጋማ አካባቢዎች ብቻ ይለማ የነበረውን የስንዴ ሰብል የግብርና አሰራር ለመቀየር በቆላማ አካባቢዎች የማላመድ ስራ ተጀምሯል፡፡ከውጭ አገር የሚመጣውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ለመተካት መስኖን በመጠቀም በሰሜን ወሎ ዞን በቆላ ስንዴ ለመሸፈን እየተሰራ ሲሆን የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል በራያ ቆቦ ወረዳ ከቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያለማውን የቆላ ስንዴ የአርሶ አደሮች ማሳ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የመስክ ጉብኝት አድርጓል፡፡ አርሶ አደሮቹም ከዚህ በፊት በሽንብራና በአገዳ ሰብሎች ተወስኖ የነበረው የግብርና ስራቸው በቆላ ስንዴ መሸፈኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ቆላማው አካባቢ በስንዴ እንዲሸፈን ምርምርና ዘር እስከ ማቅረብ አጋር ሁኖ እየሰራ መሆኑንና በደጋማ አካባቢዎች ይለማ የነበረው የስንዴ ሰብል በቆላማ አካባቢዎች መልማቱ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ገዛኽኝ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እንድሪስ ፈንታው የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል በቂ የሆኑ ማሳያዎችን ተግባራዊ በማድረጉ ለቆላማ አካባቢዎች ስንዴን ማልማት የሚስችል ተሞክሮ ማገኘታቸውን ገልፀው እንደ ዞን ሰፊ ማሳ ለማልማት የዘር እጥረት የገጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ ላለፉት 34 ዓመታት ከ60 በላይ ዝርያዎችን በማፍለቅ፣ በማላመድና በማስፋት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ዘገባው የሰሜን ወሎ ኮሙኒኬሽን ነው::




ከውጭ ሀገር የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እየሠራ መሆኑን የአዴት የግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአዴት የግብርና ምርምር ማዕከል ከአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የበጋ መስኖ በኩታገጠም ባለማው የስንዴ ማሣ ላይ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል። ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ችባችባሳ ቀበሌ በ27 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እያለማ ነው። ምርምር ማዕከሉ 65 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል። ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት 40 ነጥብ 5 ኩንታል የቀቀባ ምርጥ ዘር ስንዴ አቅርቧል። የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ አበዋ በውጭ ምንዛሬ የሚመጣን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የመስኖ ልማት ባለባቸው ሁሉም ወረዳዎች ላይ የስንዴ ቅድመ ማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ስንዴን በመስኖ ለማልማት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በመለየት ለአርሶ አደሮች ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል። ምርምር ማዕከሉ ከአፈር ማዳበሪያ ውጭ ሁሉንም ግብዓት በነጻ ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ቁጥር ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ማዕከሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በባሕር ዳር ዙሪያ እና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች 214 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እያለማ ነው ብለዋል። በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ 26 ነጥብ 25 ሄክታር መሬት ላይ የዘር ብዜት መሆኑንም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጥላዬ ተክለወልድ በክልሉ ከሚገኙ ሰባት የምርምር ማዕከላት ውስጥ አምስት ማዕከላት በሰብል ላይ ምርምር እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። እ.ኤ.አ በ2023 ከውጭ ሀገር የሚገባውን የስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን የተያዘውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት በአማራ ክልል 13 ሺህ ሄክታር ያህል መሬት በመስኖ ስንዴ ተሸፍኗል ብለዋል። አርሶ አደር ክንዴ አገኝ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ባመጣው በመስኖ ስንዴ ምርት ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነግረውናል። ካሁን በፊት ስንዴ ቢያርቱም ሂደቱን ጠብቀው ባለመዝራታቸውና ተገቢውን ግብዓት ባለመጠቀማቸው ውጤታማ እንዳልነበሩም ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት ተገቢውን ግብዓት በመጠቀማቸው እና የባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው የተሻለ ምርት ይጠብቃሉ። ሌላኛው አርሶ አደር ሀብታሙ ደመም በመስክ ምልከታው ላይ ተሳታፊ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ሀብታሙ የእርሻ ማሳቸው ውኃ ገብ ባለመሆኑ ስንዴን በመስኖ ማምረት አልቻሉም፡፡ በጉብኝቱ ላይ መሳተፋቸው ግን በቀጣይ የጉድጓድ ውኃ ቆፍረውም ቢሆን ስንዴን በመስኖ ለማልማት ሀሳብ እንደመጣላቸው ነግረውናል፡፡ የመስክ ምልከታውም ስንዴን ለማልማት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል። በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ በ2013 ዓ.ም 1 ሺህ 98 ሄክታር መሬት ስንዴ በመስኖ እየለማ መሆኑን ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ዘገባው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ነው::
የቆላ ስንዴ ልማት ፕሮጀክት በአርሶ አደሩ ዘንድ ትልቅ ተስፋን ይዞ መጥቷል
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የቆላ ስንዴ በመስኖ እየለማ ሲሆን አፈጻጸሙን ለመገምገምና ልምድ ለመለዋወጥ በዞኑ ኤፍራታና ግድም ወረዳ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የመስክ ቀን ተካሂዷል፡፡ በመስክ ቀኑ የበጋ ስንዴ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተሻለ ተስፋ ይዞ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ አርሶ አደር ኑሬ ወርቁ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ የአላላ ቀበሌ ነዋሪ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ቀይ ሽንኩርትና በቆሎ በመስኖ ያለማ እንደነበር የሚገልጸው አቶ ኑሬ በዚህ አመት ግን በመንግስት በኩል በካባቢያቸው ስንዴን በመስኖ እንዲለማ በተሰጠው ምክረ-ሀሳብ መሰረት የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል፣ የዞንና የወረዳ ግብርና ባለሙያዎች ባደረጉለት ድጋፍ ስንዴን በመስኖ እያለማ መሆኑን ይናገራል፡፡ በአካባበው ስንዴ በመስኖ ለምቶ ስለማያውቅ መጀመሪያ አካባቢ ተጠራጥሬ ከበቆሎ ጋር ቀላቅየ ዘርቸው ነበር፤ በኋላ ግን የስንዴው ቡቃያ የተሻለ ሆኖ ስላገኘሁት በቆሎውን አስወግጀ ስንዴውን በአግባቡ መንከባከብ ጀመርኩ፡፡ አሁን በደጋው አካባቢ በመኸር ከሚዘራው ስንዴ ባልተናነሰ ሰብሉ ጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል የሚለው አርሶ አደር ኑሬ የተሻለ ምርት እንደሚያገኝ ትልቅ ተስፋ እንዳለውና በቀጣይም የስንዴ ልማት ስራውን የበለጠ ለማስፋት እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ ሌላው የአለላ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው አቶ ሰለሞን ታምራት ከዚህ በፊት በመምህርነት ሙያ ያገለግል የነበረ ሲሆን አሁን ግን ፊቱን ወደ ግብርና አዙሯል፡፡ አቶ ሰለሞን የግብርና ባለሙያዎች ስንዴን በመስኖ እንዲዘሩ በሰጧቸው ምክረ-ሀሳብ መሰረት ወደ ስራ መግባቱን ገልጿል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ በስራው ለመሳተፍ በርካታ አርሶ አደሮች ተመዝግብው ነበር የሚለው አቶ ሰለሞን በኋላ ላይ በመጠራጠር በርካቶች ደፍረው መግባት አልቻሉም፤ እኔ ግን ሞክሬ ማየት አለብኝ በማለት ግማሽ ሄክታር የሚጠጋ መሬቴን በስንዴ ሰብል ሸፍኛለሁ ብሏል፡፡ በዚህም ሰብሉ ጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝና ወደ ፊትም ስራውን የበለጠ ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኑን አቶ ሰለሞን ተናግሯል፡፡ የደብረ-ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አዳሙ ሞላ በሰሜን ሸዋ ዞን ስንዴ በመስኖ እንዲለማ ምርምር ማዕከሉ ከባለ ድርሻ አካለት ጋር በመቀናጀት ልዩ ልዩ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ “ቀቀባ” የተሰኘ የስንዴ ዝርያ በቆላ አካባቢዎች በመስኖ እንዲለማ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ሌሎች ለቆላ ተስማሚ የሆኑ የስንዴ ዝርያዎችን ለመለየት ጎን ለጎን የምርምር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናረዋል፡፡
በምርምር ማዕከሉ ድጋፍ በዞኑ በኤፍራታና ግድም፣ አንጾኪያ ገምዛ እና ቀወት ወረዳዎች 98 አርሶ አደሮች(ከዚህ ውስጥ 4ቱ ኢንቨስተሮች ናቸው) 53 ሄክታር መሬት የቆላ ስንዴ በመስኖ እያለሙ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንዶሰን ደምሴ በበኩላቸው በዞኑ ከጤፍ ቀጥሎ ስንዴ በከፍተኛ ደረጃ በመኸር የሚመረት ሰብል መሆኑን ገልጸው በመኸር እርሻ ከ113ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመዝራት እስከ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ሲገኝ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጅ ቆላማ አካባቢዎች ስንዴን አምርተው እንደማያውቁ የሚገልጹት ምክትል ኃላፊው በዚህ አመት በመንግስት በተጀመረው ሀገራዊ ፕሮጀክት መሰረት ስንዴን በቆላማ አካባቢዎች ማምረት እንደሚቻል ማሳየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ወደ ስራ ሲገባ በአርሶ አደሩ በኩል እንዴት ስንዴ ቆላ ላይ ይለማል በሚል አሰራሩን ላለመቀበል ችግሮች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ወንዶሰን አሁን ግን ለምቶ ሲታይ በርካታ አርሶ አደሮች ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል፡፡ የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የጀመረውን ተሞክሮ በመውሰድ የዞኑ ግብርና መምሪያ ስራውን በ11 ወረዳዎች ላይ መጀመሩን የገልጹት አቶ ወንዶሰን በ3ሺህ 328 ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት ታቅዶ የዘር እጥረት በመግጠሙ በ653 ሄክታር መሬት ላይ የቆላ ስንዴ እየለማ መሆኑን እና 1ሺህ 368 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ዘር በማቅረብ፣ ልዩ ልዩ ሙያዊ ድጋፎችን በማድረግ በኩል የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉንም ምክትል መምሪያ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በመስክ ቀኑ የተሳተፉ አርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት ሁሉም አካላት የየድርሻውን ኃላፊነት መወጣት እና ተቀናጅቶ መስራት፣ ያሉ የውሃ አማራጮችን በአግባቡ መጠቀምና የተሻሉ ቴክኖሎጅዎችን ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ እንደ ሀገር የተያዘውን በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብ ማሳካት ይቻላል ብለዋል፡፡








Please click here to watch this video
የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግማሽ ዓመት የዕቅድ የአፈፃፀም ግምገማ አካሄደ::
ኢንስቲትዩቱ በስድስት ወር ዉስጥ ለመተግበር አቅዶ የፈፀማቸዉን ስራዎች አፈፃፀማቸው ያለበትን ደረጃ የተቋሙ ሰራተኞች በተገኙበት ግምገማ አካሄዷል፡፡ በ2013 ዓ/ም በጀት ዓመት በዋናነት በሰብል፣ በእንስሳት፣ በአፈርና ውሃ፣ በማህበራዊ ምጣኔ ሃብትና ግብርና ኤክስቴንሽን፣በደን፣ በቴክኖሎጅ ብዜትና ዘር ምርምር የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በህዝብ ግንኙነትና አጋርነት በፋይናስ፣ በሰው ሀብት ልማት፣ በግንባታና ጥገና እንዲሁም በክትትልና ድጋፍ የተሠሩ ሥራዎችንም በሪፖርቱ ተካተው ቀርበዋል፡፡ በእቅዱ መሰረትም ችግር ፈች እና ፍላጎት ተኮር የግብርና ቴክኖሎጅዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን ማፍለቅና ማላመድ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 142 ቴክኖሎጂዎችን ለማዉጣት የሚያስችሉ 564 ስራዎችን ለማከናወን ታቅዶ 536 (95.04%) መከናወን የተቻለ መሆኑን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ የመነሻ ቴክኖሎጅ ብዜትንም ለምግብ ዋስትና፣ ለገበያና ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃዎች የሚያገለግሉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን የማባዛት ስራ በተመለከተ በበጀት ዓመቱ በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው 202.94 ሄ/ር በግማሽ የበጀት ዓመቱ 244.39 ሄ/ር መከናወኑን ከቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቴክኖሎጅን ለማስተዋወቅ በግማሽ የበጀት ዓመት ለ17ሺህ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ለማስተዋወቅ ታቅዶ ለ12ሺህ 181 ተሳታፊዎች ልዩ ልዩ ቴክኖሎጅዎችን የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡አፈፃፀሙ ያነሰበት ምክንያት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አርሶአደሮችንና ባለሙያዎችን በአንድ ቦታ ስብስቦ ለማሰልጠን ባለመቻሉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በግምገማው ተቋሙ የበጀት አመቱ እቅድ አፈፃፀም በተገቢዉ መንገድ ያሳካ ቢሆንም ባልተደረሰባቸዉ የእቅድ አፈፃፀሞች ላይ እስከ በጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ለመፈፀም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች በዕለቱ በቀረበው ሪፖርት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው የጋራ መግባባት ተደርሶባቸዋል፡፡ወደፊትም የሚጠበቅባቸውን በቅንነት እና በተባባሪት መንፈስ ለመፈፀም ዝግጅነታቸውን ገልፀዋል፡፡በመጨረሻም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላዩ ተክለወልድ ሠራተኞች የተቋሙን ተልዕኮ በትክክል በመገንዘብ ለስኬቱ በአንድነት እንዲረባረቡ፣ የሥራ ዲስፕሊንን በማክበርና መመሪያን በመጠበቅ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል::
የስራ ኃላፊዎችን ቀልብ የሳበው ምልከታ በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት
ትላንት እሁድ ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ግቢ ውስጥ ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች በጠዋቱ ተገኝተዋል፡፡ በግቢው ውስጥ የመገኘታቸው ዋና ምክንያት ደግሞ በኢንስቲትዩቱ ውስጥ በቲሹካልቸር የሚሰሩ ስራዎችን ለመመልከት ነበር፡፡ የስራ ኃላፊዎቹ “ምን ስራ ሊያሳዩን ይሆን” የሚል ጥያቄ በአዕምሮአቸው ውስጥ ሳያጭርባቸው አልቀረም፡፡ የተጠሩ እንግዶች ከመጡ በኋላ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላየ ተክለወልድ እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ምን እንደሚጎበኝ ገለጻ አደረጉ፡፡ በመቀጠል የስራ ኃላፊዎቹ ያመሩት በክልሉ በሚገባ ስራውን እየከወነ ወደ ሚገኘው የኢንስቲትዩቱ ቲሹ ካልቸር ላብላቶሪ አመሩ፡፡ በር ላይ ሲደርሱ ሁሉም ጫማ እንዲያወልቁ ተጠየቁ፤ “እንዴ ለምን” የሚል ጥያቄ ሁሉም አነሱ፡፡
የቲሹ ካልቸር ተመራማሪዎች ከውጭ ባዕድ ነገሮችና የዕጽዋት በሽታዎች አብረው እንዳይገቡ ጥንቃቄ ለማድረግ መሆኑን ገለጻ አደረጉ፡፡ በዚህም እንግዶቹ ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ ነጠላ ጫማ፣ ነጭ ጋወን እንዲለብሱና እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያጸዱ ተደረገና ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ በመቀጠል የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር ኤርሚያስ አባተ እና የቲሹ ካልቸር ተመራማሪዎች ስለ አጠቃላይ አሰራሩ ገለጻ አደረጉ፡፡ እንዴት የአትክልትና ፍራፍሬ እጽዋትን በተለይም ድንችን ምርታማነቱን እና ጤንነቱን ጠብቆ ማምረት እንደሚቻል እና በላብላቶሪው ውስጥ ምን አይነት ሳይንሳዊ ስራዎች እንደሚሰሩ ገለጻ ሲደረግ ሁሉም በአግራሞት ገለጻውን ይከታተላሉ፡፡ አብዛኞቹም “እንዴ እኛ እኮ እንደዚህ እንደምትሰሩ አናውቅም” አሉ፡፡ ብዙዎች እንግዳ ሆኖባቸዋል፤ ክልሉ ውስጥ እንዲህ አይነት ላብላቶሪ እና የምርምር ስራ እንደሚሰራ በቂ ግንዛቤው አልነበራቸውም፡፡ በመቀጠል የስራ ኃላፊዎቹ ከላብላቶሪው በመውጣት በሰው ሰራሽ ዘዴ ከላብላቶሪ የወጡ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች ወደ ሚላመዱበት ቤተ-ሀመልማል በማምራት ተዘዋውረው ተመለከቱ፡፡ እዚህም ባለው ስራ እጅግ የተገረሙ ሲሆን የሚሰሩ ስራዎች ለክልሉ ህዝብ ትልቅ ተስፋ የሚሆኑ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡
በኢንስቲትዩቱ ግቢ የነበረው ምልከታ ከተጠናቀቀ በኋላ የስራ ኃላፊዎቹ በዋናነት ሰብል ላይ አተኩሮ ምርምሩን ወደ ሚያካሂደው የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ነው ያመሩት፡፡ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የድንች ምርምር አስተባባሪና ዋና የብዜት ማዕከል ሲሆን በግቢው ውስጥ ባሉ በርካታ ቤተ-ሀመልማሎች አማካኝነት የተለያዩ የድንችና ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ እየተሰራ መሆኑን ሲመለከቱም ሌላ መገረም ፈጥሮባቸዋል፡፡ በመቀጠል የማዕከሉን አዲስ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን ደረጃውን የጠበቀ ህንጻ ተመለከቱ፡፡ ከዛም የመስክ ምልከታውን አስመልክቶ አጭር ውይይት ተደረገ፡፡በውይይቱ ሁሉም የስራ ኃላፊዎች የተመለከቱትንና ኢንስቲትዩቱ እየሰራቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎች ግብርናውን ለማዘመንና የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው፣ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሀሳባቸውን ሰጡ፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መለስ መኮንን ኢንስቲትዩቱ የሚሰራቸው ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው ውጤታማ ስራ ለመስራት ግን ሁሉም በግብርና ላይ የሚሰሩ ተቋማትና አጋር አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዶ/ር መለስ የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ህዝብና ውሳኔ ሰጭ አካላት ሊያውቋቸው እንደሚገባም የተናገሩ ሲሆን ግብርናውን በምርምር ካልተደገፈ የትም መድረስ አይቻልም፤ ተቋም ግንባታ እና ተናቦ መስራት እናተኩር የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመስክ ምልከታው የተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችም የምርምር ተቋሙ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ እንደየተቋማቸው ኃላፊነት የሚችሉትን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
የወተት ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የደብረ-ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
ምርምር ማዕከሉ እየጨመረ የመጣውን የወተት ፍላጎት ለማሟላትና በደብረ ብርሃን አካባቢዎች እየተስፋፉ የሚገኙትን የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት ለመሸፈን ልዩ ልዩ ስልቶችን ነድፎ እየሰራ ይገኛል፡፡ በምርምር ማዕከሉ የእንስሳት ምርምር ቴክኖሎጅ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ የሻምበል በሱፈቃድ ምርምር ማዕከሉ የተሻለ የወተት ምርት የሚሰጡ ላሞች ዝርያን ለማሻሻል ለአርሶ አደሮች በማህበር በማደራጀት የተሻሻሉ ኮርማዎችን በመስጠት፣ በተፈጥሮአዊና በሰው ሰራሽ ዘዴ የማዳቀል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህም ምርምር ማዕከሉ በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ የተሻሻሉ ኮርማዎችን ለአርሶ አደሮች የሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ የሻምበል በቅርቡም በወረዳው ጨኪ ቀበሌ 1 የተሻሻለ ኮርማ በወተት ምርት ለተደራጁ አርሶ አደሮች ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ምርምር ማዕከሉ የወተት ላሞችን ዝርያ ከማሻሻል በተጨማሪ የወተት ምርትን የሚያሳድጉ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀም ይገኛል፡፡ ይህም የእንስሳትን አመጋገም በማሻሻል የወተት ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የእንስሳት ጤናን ማሻሻል ሌላው ምርምር ማዕከሉ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት መሆኑን የጠቀሱት አቶ የሻምበል የእንስሳትን ጤንነት በአግባቡ ለመጠበቅ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ስራዎች ከዝርያ ማሻሻልና መኖ አቅርቦት ስራዎች ጋር እኩል ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የወተት ምርትን ለማሻሻል ምርምር ከሚሰራባቸው አካባቢዎች መካከል የአንጎለላ ጠራ ወረዳ አንዱ ሲሆን በወረዳው ጨኪ ቀበሌ በወተት ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ምርምር ማዕከሉ የወተት ምርትን ሊጨምሩ የሚችሉ ቴክኖሎጅዎችን እያቀረበላቸው መሆኑን ገልጸው ለተደረገላቸው የኮርማ ድጋፍም ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡
የደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የተሻሻሉ የበግ ዝርያዎችን በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል የስጋ ምርትን ለማሳደግ እየሰራ ነው::
የደብረ-ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል በሰሜን ሸዋ ደጋማ አካባቢዎች የሚገኘውን የሀገረሰብ በግ ዝርያ የተሻለ የስጋ ምርት በመስጠት በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆነው ዶርፐር የተሰኘ የደቡብ አፍሪካ በግ ዝርያ ጋር በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ውጤት ለማገኘት እየሰራ ይገኛል፡፡በምርምር ማዕከሉ የእንስሳት ተመራማሪና የእንስሳት ምርምር ቴክኖሎጅ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ የሻምበል በሱፈቃድ ምርምር ማዕከሉ ባደረገው ጥናት ንጹህ የዶርፐር በግ ዝርያዎችን በሰሜን ሸዋ ዞን ደጋማ አካባቢዎች ከሚገኙ የሀገረሰብ በግ ዝርያዎች ጋር በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል 72 በመቶ ውጤታማ እርግዝና ማስገኘት ተችሏል ብለዋል፡፡ አሰራሩ በተፈጥሮ ማዳቀል ዘዴ የሀገረሰብ በጎችን በመግዛትና በማዕከል ውስጥ በንጹህ ዶርፐር በማዳቀል የሚወለደውን 50 በመቶ የዶርፐር ድቃላ አውራ ለአርሶአደር በማሰራጨት ሲሰራ የነበረውን የዝርያ ማሻሻል ስራ ወጭ ከመቀነስ በተጨማሪ 50 በመቶ የዶርፐር ድቃላ ግልገል በአርሶአደር ይዞታ ለማግኘት ይፈጅ የነበረውን 5-6 ትውልድ ወይንም ከ12-14 ዓመት ማስቀረት የሚያስችል መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
አንድ የዶርፐር አውራ በአንድ የተፈጥሮ ድቀላ ለአንድ በግ እርግዝና ሊያውለው የነበረውን ዘር በመሰብሰብ በአማካኝ ከ30 እስከ 40 ለሚሆኑ እንስት በጎች በመስጠት በሰው ሰራሽ ማዳቀል ዘዴ በመጠቀም በአጭር ጊዜ በርካታ የዶርፐር ዲቃላ በጎችን መስጠት እንደሚቻልም ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መነሻነት በ2013ዓ.ም ምርምር ማዕከሉ በሰሜን ሸዋ ደጋማ አካባቢዎች 1600 በጎችን በሰው ሰራሽ ዘዴ ከዶርፐር በግ ዝርያ ጋር ለማዳቀል አቅዶ እየሰራ ሲሆን በቀጣዮቹ 10 አመታት ከመንዝ በስተቀር የሰሜን ሸዋ ደጋማ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ በዶርፐር ዲቃላ በጎች ለማዳረስ መታቀዱን አቶ የሻምበል ገልጸዋል፡፡ይህም እየጨመረ የመጣውን የስጋ ፍላጎት ለማሟላትና የአለም አቀፍ ገበያን የግብይት ደረጃ ማሟላት የሚችሉ በጎችን ለማግኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡በመንዝ አባቢዎች በመረጣ የተሻሻሉ የመንዝ በግ አውራዎችን ከመንዝ እንስት በጎች ጋር በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል በመረጣ የዝርያ ማሻሻል ስራውን ለማፋጠንም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በ2013 በጀት አመት 2600 በጎችን ለማዳቀል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይህ አሰራር የሀገረሰብ ዝርያ የሆኑት የመንዝ በጎች ዝርያቸው ሳይከለስ በመረጣ በአጭር ጊዜ ዝርያቸው እንዲሻሻል ለማድረግ እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡