የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ መስራት የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ከመጠበቁም በላይ ኢኮኖሚያው ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት አማራ ክልልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች በየዓመቱ ከ200 እስከ 300 ቶን በሄክታር የአፈር ክለት ይከሰታል፡፡ ለአፈር ክለቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፤ የህዝብ ቁጥር መጨመር፤ የደን መመንጠር፤ ልቅ ግጦሽ፤ የመሬቱ ወጣገባነትና ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ፤ ጥንቃቄ የጎደለው የእርሻ አስተራረስና ጊዜያዊ የግብርና ምርትን ለማሳደግ ሲባል የሚከናወን የእርሻ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በአማራ ክልል በዝናብና ጎርፍ ምክንያት የሚፈጠር የአፈር እና ውሃ ክለትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር አፈርን እና ውሃ ለማቀብ የሚረዱ የአካባቢን መልክአምድራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ የተለያዩ እርከኖችን መስራትና ከአሁን በፊት የነበሩትንም ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ የሚሰሩ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑም በተፋሰስ ደረጃ ለሚከናወኑ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች የአዋጭነት ጥናት ማከናወን እና ለአርሶ አደሩ ማሳወቅ የተፋሰሶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡
ለአብነት የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአፈርና ውሃ ዘርፍ በኩል በተፋሰስ ደረጃ የሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራዎችን ዘላቂ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ የአዋጭነት ጥናት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጉማራ ማክሰኝት ኩታ ገጠም ተፋሰሶች ላይ ለስምንት ዓመታት ጥናት አከናውኗል። የጥናቱ ውጤት እንደሚያመላክተው፡-
Ø የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በመሰራቱ ምክንያት የአፈር ክለት በ46.8% በዓመት ቀንሷል፡፡ በዚህም መሰረት ተፋሰስ ላይ የአፈር ክለቱ በአመት 9.98 ቶን በሄክታር ሲሆን ባልተሰራበት ተፋሰስ ግን በአመት 18.76 ቶን በሄክታር ነው፡፡
Ø የኦርጋኒክ ንጥረ-ነገሮች ክለት ደግሞ በ61.3% በዓመት ቀንሷል፡፡ ይህም የአፈርና ውሃ ጥበቃ በተሰራበት ተፋሰስ በአመት በሄክታር የኦርጋኒክ ንጥረ-ነገር ክለት ሲኖር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባልተሰራበት ተፋሰስ 420.18 ኪሎግራም በሄክታር ሆኗል፡፡
Ø የናይትሮጂን ክለት በ57.97% በዓመት ቀንሷል፡፡ ይህም ክለቱ እርከን በተሰራበት ተፋሰስ በአመት 12.653 ኪሎግራም በሄክታር በዓመት ሲሆን እርከን ባልተሰራበት ተፋሰስ ደግሞ 30.103 ኪሎግራም በሄክታር መሆኑን ያመለክታል፡፡
Ø በተመለከተ በ65.86% በዓመት ቀንሷል፡፡ እርከን የተሰራበት ተፋሰስ በአመት 0.16 ኪሎግራም በሄክታር የፌስፎረስ ክለት ሲኖር የአፈርና ውሃ እቀባ ባልተሰራበት ተፋሰስ ደግሞ በሄክታር የፎስፎረስ ክለት ተመዝግቧል፡፡
Ø ከምርታማነት አኳያም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ በተሰራበት ተፋሰስ ውስጥ የጤፍ ምርት በ13% በዓመት ጨምሯል፤ የማሽላ ምርት በ19.4% በዓመት ጨምሯል፤ የሽምብራ ምርት በ19.42% በዓመት ጨምሯል፡፡ ስለሆነም ከዚህ የጥናት ውጤት መረዳት እንደሚቻለው ቀጣይነት ያለው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ስራ መስራት የአፈር ክለትን ለመቀነስ እና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ጉልህ ድርሻ መኖሩን ነው፡፡
