የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመስኖና ደን ምርምር አጀንዳዎች ቀረፃ እና የተጠናቀቁ ሙከራዎች ግምገማ አውደጥናት ከጥቅምት 10-13/2019 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መካሄዱን አስታወቀ
አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላዩ ተ/ወልድ እንደተናገሩት የአማራ ክልል ከሀገሪቱ 35 ፐርሰንት(%) የሆነውን የግብርና ምርት የሚያበረክትና በውሃ ሃብት ልማት እና በሌሎች ብዝሃህይወት ሃብቱ ባለፀጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ እንደመሆኗ መጠን አማራ ክልልም የኢትዮጵያ የውሃ ማማ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ዓመቱን በሙሉ ብዙ የሚፈስሱ ወንዞች ቢኖሩም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳልዋሉ ተናግረዋል፡፡
ክልሉ የበርካታ ብዝሀ ሕይወት፣ የተለያዩ መልካ ምድራዊ ስፍራዎች ፣ ከ4.4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት ከዚህ ውስጥ አንድ አራተኛው ለመስኖ አመች የሆነ፣ ለደን ልማት የሚውሉ በርካታ የደን ሀብቶች (የተፈጥሮ ደን፣ የቆላና በረሃ ደን (ሙጫ እና ዕጣን)፣ የቀርከሃ ዛፍ፣ ከፍተኛ የተማረ የሰው ሀይል እና ታታሪ አርሶአደሮዎች ሁሉ መገኛ መሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡ ለግብርና እና ለደን-ተኮር ልማት እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ክልሉ ተስማሚ መሆኑን ጠቅሰው የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም አንዳንድ የደን ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተቋቋሙ እንደሚገኙም አክለው ተናግረዋል ፡፡
የመስኖ እና የደን ልማቶች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፣ ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት (የደን ምርቶች፣ ዘይት፣ ስንዴ ወዘተ)፤ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማምረት እና ለአገር ውስጥ ግብርና ኢንዱስትሪ ግብዓት ምንጭ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ለመስኖ እና ለደን ቴክኖሎጂዎችን ማመንጨት (ማፍለቅ) እና ማላመድ በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ህይወት ለመለወጥ እና የኑሮ ሁኔታቸውን ለማሻሻል እንዲሁም አካባቢን ለመከላከል አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ ትልልቅ ፣ መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ልማት ግንባታዎች መገንባታቸውን ተከትሎ በመስኖ የሚለማው አካባቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አውስተው የዓለም የግብርና ልማት ተራድኦ ድርጅት (IFAD) እና የግብርና ዕድገት ፕሮግራም/AGP/ የርብ እና መገጭ ግድቦች እንዲሁም ሌሎች በርካታ ትናንሽ ግድቦችም በመገንባት የመስኖ አቅርቦትና አጠቃቀም የማሻሻል፤ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትን የማሳደግና ድህነትን ለመዋጋት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
የመስኖ ልማትን ማስፋፋት በዓመት አንድ ጊዜ በዝናብ ከሚገኘው የግብርና ምርት በተጨማሪ በአጠቃላይ ምርትን ማሳደግ ስለሚያስችል ጠቀሜታው የጐላ ሲሆን የተሻሻሉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ዘለቄታዊ የሆነ የግብርና ምርት እድገትን ማስገኘት ያስችላል ብለዋል፡፡ ለዚህ ዓላማ መሳካትም የተቀናጀ የመስኖ ምርምር ማካሄድ የተሻሻሉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጅዎችን ለማመንጨት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ አርሶ አደሮች እና የኤክስቴንሽን ኤጀንሲዎች የቴክኖሎጂ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ በዝናብ ወቅት ከሚመረቱ የሰብል ዓይነቶች በተጨማሪ በመስኖ ሊመረቱ የሚችሉ ሌሎች የሰብል አይነቶችን ለማምረት እንዲሁም ከፍተኛ ምርት ሊሰጡ የሚችሉና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የሰብል ዝርያዎችን፤ በመስኖ ለሚለሙ የሰብልና መኖ ዝርያዎች የተሻሻሉ የውሃ አጠቃቀምና የመስኖ ውሃ ማጠጫ ጊዜን፤ ውሃ ቆጣቢ የሆነ ዓመታዊ የሰብል አመራረትና የሰብል ፈረቃ ስርዓትን እንዲሁም ለገበያ አዋጭ የሆነ የመስኖ ግብርና ስርዓትን ፤ ለእንስሳት ምርት ማነቆ የሆነውን የመኖ እጥረት ከመሰኖ አውታሮችና ከሰብል አመራረት ስርዓት ጋር በማጣመር የእንስሳት ምርት ለማሳደግ የሚያስችል መፍትሄ ለመፈለግ፤ ባህላዊ እና ዘመናዊ የመስኖ ልማት አውታሮች ውጤታማነታቸውንና የሚያስከትሉትን ስነ ምህዳራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችን ለመለየትና ወቅቱን የጠበቀ መፍትሄ ለመሻት፤ በቅድመና ድህረ ምርት የሚከሰቱ የምርት መጠንና የምርት ጥራት ችግሮችን ለማሻሻል የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን ወደ ተጠቃሚ ለማድረስ የሚያስችሉ የቴክኖሎጅ ሽግግር ስርዓቶችን ለመዘርጋት የምርምር ስራዎች ተሰርተዋል፤ በመሰራትም ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
በደን ልማት ዘርፍ የእንጨት እና እንጨት-ነክ ያልሆኑ ምርቶች እንዲሁም በአጠቃላይ ሥነ-ምህዳራዊ የአገልግሎት ፍላጎቶች በርካታ መሆናቸውን አውስተው እንደ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ እና ሌሎች የክልሉ ዞኖች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ለእነዚህ ፍላጎቶች ደን በመትከል ምላሽ እየሰጡ ቢሆንም እየጨመረ የመጣው ፍላጎት በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ደኖች ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍና ፍላጎቶችን ለማሟላት ዕፅዋቶችን የማልማት እና ብዝሀ- ህይወትን ወደ ነበረበት ለመመለስ እንዲሁም ግብርናን ዘላቂ ለማድረግ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት ረገድ ሰፊ የደን ምርምር ሥራ ይጠብቀናል ብለዋል፡፡ ለእነዚህ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት የአጭር እና የረጅም ጊዜ የምርምር ዕቅድ እንዲሁም ለመሠረተ ልማት እና ለሰብአዊ ሀብት ልማት የሚውል አጠቃላይ ስትራቴጂ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በዚህ አግባብ የግብርና ልማት ችግሮች እና የክልሉ መንግስት የልማት ፍላጐት በሆኑት ዙሪያ የምርምር አጀንዳዎችን በመቅረፅ፤ ዕቅዶቹንም ገምግሞ በማጽደቅ ወደ ተግባር ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ ሁሉንም ተሳታፊዎች በተለይም ለምርምሩ ውጤት መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱት ተመራማሪዎች እና ከአ.አ ድረስ በመምጣት የክልሉ ምርምር ግምገማ አካል ለሆኑት ምስጋና አቅርበዋል::
በአውደ ጥናቱ የመጀመሪያ ቀን በ3 የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በተጋባዠ እንግዶች ጥናታዊ ፁሁፎች ከቀርቡ በኋላ ዶ / ር ኤርሚያስ አባተ የግብርና ምርምር ኢንስቲቱት ም/ዋ/ዳይሬክተር የሆኑት በቀረቡ ጥናታዊ ፁሁፎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ አስተያየቶችን እና ግልፅ ያልሆኑ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ ለተሳታፊዎቹ ዕድል ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ቀርበው ለተነሱ አስተያይቶችና ጥያቄዎች በአቅራቢዎች ተገቢው ምላሽ ተሰጧል፡፡
አውደ ጥናቱ በኢንስቲትዩቱ ስር በሚገኙት የምርምር ማዕከላት አማካኝነት በተለያዩ ዘርፎች ማለትም በሰብል፣ በእንስሳት፣ በአፈርና ውሃ፣ በደን እና በሶሺዮ-ኢኮኖሚክስ ተከፍለው የምርምር ስራዎች የተገመገሙ ሲሆን በሰብል 59 ሙከራዎች ቀርበው 44 የፀደቁ፣ በአፈርና ውሃ 48 ቀርበው 24 የጸደቁ፣ በእንስሳት ከ22 ሙከራዎች 21 የፀደቁ፣ በደን ከ81 ሙከራዎች ውስጥ 66 የፀደቁ፤ በሶሺዮ-ኢኮኖሚክስና ኤክስቴንሽን ዘርፍ ከ37 ሙከራዎች ውስጥ 30 ፀድቀዋል፡፡ በቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር በቅድመ- መስራች በ1.7ሄክታር ንፁህ ዘር 13.5 ኩንታል፤ በመስራች በ 1.58 ሄክታር ንፁህ ዘር 28.1 ኩንታል፤ በአባዥ ዘር በ6.3 ሄክታር 87.58 ኩንታል መባዛቱ በአውደጥናቱ ተገምግሟል፡፡
በአውደ ጥናቱ ከፍተኛ ሳይንቲስቶች ፣ ከዩኒቨርሲቲ የመጡ መምህራን፣ ከዓለም አቀፍ ፣ ከፌዴራል እና ከክልል ምርምር ተቋማት የመጡ ተመራማሪዎች ፣ ከግብርና ትራንፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ከጀርመን ተራድዕ ድርጅት፣ ከአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት፣ ከቆጋ መስኖ ልማት ጽ/ቤት፣ ከአነስተኛ ጥቃቅን መስኖ ልማት ድጋፍ ድርጅት፣ ከግብርና ቢሮ፣ ከአማራ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ቢሮ ከዓባይ ተፋሰስ ባለስልጣንየመጡኃላፊዎችእናባለሙያዎችተሳትፈዋል፡፡


