የከተማ ግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የድርብርብ ግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ነዋሪዎች የስራ ዉጤት ተጎበኘ
የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የከተማ ግብርናን ተደራሽ ለማድረግ ከህብረተሰቡ መካከል ፈቃደኛ ግለሰቦችን መልምሎ በማሰልጠንና ወደ ስራ በማስገባት ግለሰቦች ያስመዘገቡትን የስራ ዉጤት የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አመራር፤ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊና የስድስቱ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚዎች በ11/8/2013 ዓ/ም አስጎብኝቷል፡፡በምርምር ማዕከሉ ድጋፍ ስልጠና ወስደዉ ወደ ስራ ከተሰማሩት መካከል የአቶ ሚካኤል ፈረደን የስራ ዉጤት በተሞክሮነት ተጎብኝቷል፡፡ ግለሰቡ ለግንባታ በተሰጠዉ ቦታ ላይ ድርብርብ የግብርና ቴክኖሎጅን በመተግበር የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ አይነቶችን ከወዳደቁ የሲሚንቶ ከረጢት እና የቀለም እቃዎችን በመጠቀም አትክልት በመትከል የምግብ ፍጆታዉን ከመሸፈኑም ባሻገር የአካባቢዉን ህብረተሰብ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ለስድስት ስራ አጥ ወጣቶችም የስራ እድል በመፍጠር ራሳቸዉን እንዲይስተዳድሩ እድል መፍጠሩን ይገልጻል፡፡ አቶ ሚካኤል አክለዉም የከተማዉ ነዋሪ በጓሮዉ የሚገኘዉን ትርፍ ቦታዎችን ለፍጃታ የሚዉሉ የግብርና ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን ይመክራሉ፡፡በመስክ ጉብኝቱ የተገኙት የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጥላየ ተክለወልድ እንደተናገሩት የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሰባት የግብርና ምርምር ማዕከላትን በማቋቋም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አልሞ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ከእነዚህ ማዕከላት ዉስጥም የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ነዉ ብለዋል፡፡
ዶ/ር ጥላየ አክለዉም የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ስነምህዳሩ ተሰማሚ ከሆኑ ሰብል አይነቶች ማለትም ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎችን እንደዚሁም ገብስ፤ ሽምብራና ሌሎች ሰብሎች ላይ በስፋት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ ይኸዉ ዛሬ ደግሞ የምንመለከተዉን ድርብርብ የምንለዉን የአመራረት ዘዴ አሰልጥኖ ወደ ስራ በማሰማራት በግለሰቦች የተገኘዉን ዉጤት እየጎበኘን እንገኛለን ብለዋል፡፡ይህ እየተመለከትን ያለነዉ ዉጤት ግብርናና ከተማ አብሮ አይሄድም የሚለዉን የተሳሳተ ግምት የሰበረ ነዉ፡፡ ግብርናን ከመሬት ዉጭ መጠቀም እንደምንችል አሳይቶናል ብለዋል:: ስለዚህ ዛሬ እዚህ ተሞክሮ ላይ የተሳተፋችሁ የክፍለ ከተማ አመራርና የከተማዉ ማህ/ሰብ ልምዱን በመዉሰድ ወደ ስራ በመግባትና ሌሎችም እንዲተገብሩት በማስረዳት ኃላፍነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ ብለዋል::የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ አስፋዉ አዛናዉ በበኩላቸዉ የከተማ ግብርና ስራዉን ከሁለት ዓመት በፊት ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተመለመሉ ፍቃደኛ ግለሰቦችን በማሰልጠን ወደ ስራ አስገብተናል ይላሉ፡፡ ዛሬ እየጎበኘን ያለነዉ የአቶ ሚካኤል የግብርና ስራም የዚህ ዉጤት አካል ነዉ ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ሰራ የጋራ ርብርብን ስለሚጠይቅ በጉብኝቱ ላይ የተገኛችሁ የጎንደር ከተማ አስተዳደር እና የክፍለ ከተማ አመራሮች ተግባሩን በትኩረት በመያዝ ህ/ሰባችን በጓሮዉ የሚገኘዉን ትርፍ ቦታ የግብርና ምርቶችን በማልማት የምግብ ፍጆታዉን እንዲሸፍን ከማገዙም በተጨማሪ የስራ እድል ፈጠራ በመሆኑ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡