ARARI

ARARI

Print PDF

የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በድንች ምች /ዋግ/ በሽታ ዙሪያ የመስክ ቀን አካሄደ

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የድንች ምች /ዋግ/ በሽታን መከላከል በባንጃ ወረዳ ካሳቸውላ ቀበሌ ያካሄው የሠርቶ ማሳያና የቅድመ ማስፋት ስራ ውጤታማ መሆኑን በ14/12/2009 ዓ/ም በቀበሌው በተካሄደው የመስክ ቀን ላይ መረጋገጡን የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስታወቀ፡፡

በመስክ ቀኑ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩ ይታፈሩ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በአገር አቀፍ ደረጃ የድንች ምርምር አስተባባሪ መሆኑን ገልፀው የምርምር ማዕከሉ ከሰባት የምርምር ማዕከላት አንዱ ከመሆኑም በላይ ተስማሚ በሆኑ ስነ-ምህዳሮች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የማውጣት የማስተዋወቅና የማስፋት ስራ እያካሄደ እንደሚገኝ በመክፈቻ ንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ምርምሩ በተለይም የግብርና ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ በማጥናት ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ቴክኖሎጅዎችን በማፍለቅና የመነሻ ቴክኖሎጅ አባዝቶ በማቅረብ በስፋት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዶ/ር ብሩ በተጨማሪ እደገለፁት የአርሶ አደሩ የቴክኖሎጅ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ምርትና ምርታማነትን ከፍ የሚያደርጉ እና ፍላጎቱን የሚያረኩ አማራጭ ቴክኖሎጅዎችን ማቅረብ የምርምሩ ድርሻ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በሰብል ምርምር ዳይሬክቶሬት፣ የበሽታና ተባይ መከላከል ምርምር ተመራማሪ የሆኑት አቶ ዋለልኝ ዘገየ እንደተናገሩት ድንች በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች በስፋት የሚመረት ሲሆን የአማራ ክልል ድንችን በስፋት ከሚያመርቱ ክልሎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተመራማሪው አክለውም ድንች በተወሰነ የመሬት መጠን ከፍተኛ ምርት ስለሚሰጥና ቀድሞ ስለሚደርስ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያለው ሚና የጎላ መሆኑን ገልፀው ነገር ግን የሰብሉ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱን ተናግረዋል፡፡ ለምርቱ መቀነስም እንደ ምክንያት የጠቀሱት የተለያዩ የድንች በሽታዎች መስፋፋትና ኋላቀር የአመራረትና የአያያዝ ችግሮች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ምርምሩ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሪደሚልድ ጎልድ የመድኃኒት ርጭት ሙከራ በማካሄድ የድንች ዋግ /ምች/ በሽታን የመፈወስ አቅም እንዳለውና አበረታች ውጤት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

በመስክ ቀኑ ተሳታፊ የሆኑ አርሶ አደሮችም በሰርቶ ማሳያው በመገኘት የተመለከቱት የሙከራ ስራ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸውና በቀጣይም መድኃኒቱን ገዝተው ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ከአዊ ዞን ግብርና መምሪያ፣ ከባንጃ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከልማት ጣቢያ ሠራተኞች፣ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደሮች በመስክ ጉብኝቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ayana

 

ayana2

 
Print PDF

የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በድንች ምች /ዋግ/ በሽታ መከላከል ዙሪያ ያካሄደው የቅድመ ማስፋት የምርምር ስራ ውጤታማ መሆኑን አስታወቀ

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የድንች ምች /ዋግ/ በሽታን በመከላከል ዙሪያ ያካሄው የሠርቶ ማሳያና የቅድመ ማስፋት ስራው ውጤታማ መሆኑን በይልማና ዴንሳ ወረዳ ጭንቁሊት ቀበሌ በ3/13/2009 ዓ/ም በተካሄደው የመስክ ቀን ላይ አስታወቀ፡፡

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩ ይታፈሩ በመስክ ቀኑ የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል በተለያዩ ሰብሎችና በተለያዩ አካባቢዎች ምርምር እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት ደግሞ ርቀት አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮችን ህይወት ለማሻሻል ተጨማሪ የምርምር ስራዎች በመስራት ተጠቃሚ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በተጨማሪም ድንች ከአያያዙና ከማዳበሪያ አጠቃቀሙ ጀምሮ እስከ ገበያ አቅርቦቱ ድረስ ጤነኝነቱ የተጠበቀ ድንች በማቅረብ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ እስከ ገቢ ምንጭነት ሊያገለግል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የድንች ተመራማሪ የሆኑት አቶ አለሙ እንደተናገሩት ድንች በአማራ ክልል ድንችን በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በአመራረት ወቅትመጅ በጭቃ እንደማይጣልና እንደማይሰበሰብ በዘር ወቅትም ንጹህ ዘር በመጠቀምና በኬሚካል ርጭት ብዙና ትልቅ ምርት ማምረት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በመስክ ቀኑ ተሳታፊ አርሶ አደሮችም በሰርቶ ማሳያው በመገኘት የተመለከቱት የምርምር ሙከራ ትልቅ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸውና በቀጣይም ተሸለውን የድንች ዝርያ እና መድሃኒት ርጭት በማካሄድ የተሻለ ምርት ለማምረት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዞን ግብርና መምሪያ፣ ከይልማና ዴንሳ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች፣ ከአጎራባች ቀበሌዎች ከአይባር ጎሽየ ጥሪ የተደረገላቸውና ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮችም በመስክ ቀኑ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

                   bretea1

                   bretea 2

 
Print PDF

                                                                   Archive of Agronomy soil science

Archive of Agronomy soil science

Archive of Agronomy soil science2. PNG

Archive of Agronomy soil science 3

Archive of Agronomy soil science 4

Archive of Agronomy soil science 5

Archive of Agronomy soil science 6

Archive of Agronomy soil science 7

Archive of Agronomy soil science 8

Archive of Agronomy soil science9

Archive of Agronomy soil science 10

 

Save

Save

Last Updated ( Saturday, 19 August 2017 08:43 )
 
Print PDF

በመተማ ንዑስ ግብርና ምርምር ማዕከል የመስክ ምልከታ ተካሄደ

በክልላችን በቅባት እህሎች እና በጭረት ሰብሎች ላይ በዋናነት ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ሃላፊነት የተሰጠው የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በስሩ በሚገኘው የመተማ ንዑስ ማዕከል አማካኝት በሰሊጥና በጥጥ ሰብሎች ላይ የሚያካደውን የምርምር ስራ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አመራሮችና ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የዞኑ ግብርና ዕድገት ፕሮግራም አስተባባሪ፣ የዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊዎችና የወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ሃላፊዎች በተገኙበት በመስክ ላይ አስጎብኝቷል፡፡ የመስክ ምልከታው ዋና ዓላማ ሰሊጥን በተመለከተ ማዕከሉ ለኢንቨስተሮች ያለውን የቴክኖሎጅ አማራጭ ማሳየትና በምርምር ማዕከሉ በሚካሄዱ ሌሎች የምርምር ስራዎችን ላይ ዕውቅና መፍጠር መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ጸዳሉ ጀምበር አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ማዕከሉ በሰብል፣ በእንስሳት፣በአፈርና ውሃ አጠቃቀምና አያያዝ እንዲሁም በደን የምርምር ዘርፎች በርካታ የምርምር ስራዎችንና ጥናቶችን በማካሄድ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ እንዳለ አውስተው የግብርና ምርታማነት ማነቆዎችን በመለየት፣ የፖሊሲ ሃሳቦችን በማፍለቅና የቅደመ ማስፋት ስራዎችንና የቅድመ ኤክስቴንሽን ሰርቶ ማሳያዎችን በማካሄድና የመነሻ ቴክኖሎጅዎችን አባዝቶ በማቅረብ ረገድ ተልዕኮ የተጣለባቸው የሶሽዮኢኮኖሚክስና ኤክስቴንሽን እንዲሁም የቴክኖሎጅ ብዜትና የዘር ምርምር ዳይሬክቶሬቶችም ያለባቸውን ሃላፊነት በመወጣት ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩ ይታፈሩ በበኩላቸው ማዕከሉ ብዙ እምቅ አቅም ባለው አካባቢ የሚሰራ በመሆኑ በተለይ በቆላማው የዞኑ ክፍል በደን፣ በእንስሳትና በሰብል ብዙ ቴክኖሎጅዎችን ማውጣትና የመነሻ ቴክኖሎጅዎችን አባዝቶ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ጠቁመው ደጋው ላይ ግን በቂ የምርምር መሬት ስለሌለው ተጨማሪ መሬት በመጠየቅ ደባርቅን ወደ ንዑስ ማዕከልነት በማሳደግ ማዕከሉ ሳይደርስባቸው የቆያቸውን አካባቢዎች በበግ፣ በድንች እና በሌሎች ቴክኖሎጅዎች መድረስ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም መተማ ቆላማውን የዞኑን አካባቢ እንዲሸፍን ታስቦ ወደ ማዕከልነት እንዲያድግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ማዕከሉ ወጣ ገባ በሆነ መንገድ ሲጓዝ ቆይቶ አሁን ላይ ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሆነና ከ7-8 ዓመት የሚፈጁ የምርምር ስራዎች በማዕከሉ ጥረት ፍሬ እንዳፈሩ አስገንዝበዋል፡፡

ከሃላፊዎች ንግግር በኋላ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ የገንዘብ ወጭንና ዘርን በመቆጠብ በመስመር ለመዝራት የሚያስችለው ስፎጊያ (SFOGGIA) የተባለው የጣሊያን መዝሪያ ማሽን የተጎበኘ ሲሆን ይህ ማሽን ራሱ ዘርና ማዳበሪያ የሚጥልና የሚሸፍን፣የራሱ አጀስትመንት ያለው፣ በሰዓት 3 ሄ/ር መሬት የሚዘራ፣የመበላሸት ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ የሆነና ሁሉንም ዓይነት ሰብሎች ለመዝራት የሚያገለግል እንደሆነ ከባለሙያ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በመቀጠልም የጥጥ ፣የአኩሪ አተር፣ የለውዝ ፣ የማሽላ፣በማዕከሉ የተለቀቀው ጎንደር 1 የሰሊጥ ዝርያ (ከ9-12 ኩንታል ምርት በሄ/ር የሚሰጥ ውሃ የሚቋቋም፣ከፍተኛ ቅርንጫፍ የማውጣት አቅም ያለው፣በጣም ነጭ ቀለም ያለው) የመሳሰሉት ሙከራዎች የተጎበኙ ሲሆን በመስመር ከተዘራው 140 ሄ/ር የባለሃብት መሬት (85 ሄ/ር ምዕራብ አርማጭሆ፣10 ሄ/ር ጠገዴ፣45 ሄ/ር ደለሎ) ውስጥ በደለሎ አካባቢ የተዘራው 10 ሄ/ር መሬት አቦሱፍ የአካባቢ የሰሊጥ ዝርያ ተጎብኝቷል፡፡

በመጨረሻም በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት አመራሮች፣ የስራ ሃላፊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ባለሙያዎችና የባለሃብቱ የእርሻ ስራ አስኪያጅ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በውይይቱ ወቅትም የሚከተሉት ነጥቦች ተነስተው የጋራ ግንዛቤ ተወስዶባቸዋል፡፡

 • ስራው በጣም ጥሩ ነው ባለሃብቱ በአነስተኛ ወጭ ብዙ ምርት እንዲያገኝ የሚስችለው ነው፡፡  
 • እስከአሁን የነበረው የሰሊጥ ምርት በዞን ደረጃ ትንሽ ነው፡፡ 6 ኩንታል ምርት በሄክታር ከተገኘ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው፤በእርግጥ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ 10 ኩንታል ምርት በሄ/ር እንዳገኘ ሪፖርት አድርጓል፡፡
 • በዞኑ በሰሊጥ የሚሸፈነው መሬት እና ምርታማነት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ስለሆነም የሰሊጥን ምርትና ምርታማነት ከመጨመር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አገርአቀፍና ክልልአቀፍ ፋይዳ ያለው ስራ እየሰራችሁ ስለሆነ ምን ያህል ስትራቴጂክ አመራር እተሰጠ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡
 • በማሽላ፣ በጥጥ ወዘተ ላይ እየሰራችሁ ነው ስለዚህ የምዕራብ ጎንደር አመራር ከእናንተ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን፡፡
 • አርሶአደሩ የባለሙያውን ምክር ነው የሚሰማው፡፡ ቀጣዩ የመስክ ቀን በሁለት ተከፍሎ ነው መካሄድ ያለበት፡፡ ባለሙያው በመጀመሪያ በአመለካከት መቀየር ስላለበት አንዱ መዘጋጀት ያለበት ለባለሙያው ሲሆን ሌላው ለባለሃብቶችና ለአጋር አካላት ይሆናል፡፡ የመተማ ግብርና ጽ/ቤት ኤክስፐርቶችንና የቀበሌ ግብርና ልማት ሰራተኞችን ጠርቶ ማስጎብኘት አለበት፡፡
 • ቋራና ምዕራብ አርማጭሆ ላይ ንዑስ ማዕከላት መተማ ላይ ደግሞ ዋናው ማዕከል ቢቋቋም ጥሩ ነው ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢዎች ሰፋፊ መሬት አለ፡፡
 • ለምንድን ነው ሁሉንም ነገር ለምርምር የምንተወው የመስክ ቀኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ለባለሙያዎች ማዘጋጀት አለበት፡፡ ሙያዊ ማብራሪያውን የምርምር ሰዎች ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛውን የመስክ ቀን ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምርምር ያዘጋጅ፡፡

በመጨረሻም ሁለት የመስክ ቀን የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ያዘጋጅ ቢባል ከፍተኛ ወጭ ስለሚያስከትልበት በሰሊጥ የአበባ ሰዓት ከነሃሴ 21-22/2009 ዓ.ም ሁሉም ወሳኝና ባለድርሻ አካላት የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትሩን ጨምሮ የሚገኙበት አንድ የመስክ ቀን እንዲዘጋጅ ከዚያ ውጭ እነደወረዳና እንደዞን የግብርና ጽ/ቤቶች የመስክ ቀን እንዲያዘጋጁ ስምምነት ላይ ተደርሶ የመስክ ምልከታው ተጠናቋል፡፡

               l4              

 
Print PDF

 

 

 

የአንዳሳ እንስሳት ምርምር ማዕከል ማሽነሪዎችን አስመረቀ 25ኛ ዓመት የእንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር የብር ኢዮቤልዩ በዓልን አከበረ

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፤ የአንዳሳ እንስሳት ምርምር ማዕከል ከውጭ ያስመጣቸውን ዘመናዊ የደሮ ምርምር መሳሪያዎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ጥሪ የተደረገላቸው ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች በተገኙበት ሃምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ በክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረውን 25ተኛ ዓመት የእንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር (25th ESAP Silver Jubilee) የብር ኢዮቤልዩ በዓል በደማቅ ሁኔታ የመስኩ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ሃምሌ 30 /2009 ዓ.ም ማክበሩን የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስታውቋል፡፡ በእለቱ የተገኙ የክብር እንግዶች፤
• ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የእለቱ የክብር እንግዳ
• ክቡር ዶ/ር ገ/እግዚአብሔር ገ/ዮሃንስ የኢፌድሪ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር የእንስሳት እርባታ ሚኒስትር ዴዕታ
• ክብርት ዶ/ር ምስራቅ መኮነን የኢፌድሪ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር፤የእንስሳት ጤና ሚኒስትር ዴዕታ
• ክቡር አቶ አለባቸው ንጉሴ የኢፌድሪ እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር፤ የግብይት ሚኒስትር ዴዕታ
• ክቡር ዶ/ር ብሩ ይታፈሩ የአማራ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
• ክቡር ፕሪንሲፓል ሳይንቲስት ዶ/ር አዛገ ተገኘ፤ በኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፍ እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ተወካይ ዳይሬክተር ጀኔራል
• ክቡር ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ በኢትዮጵያ የመሬትና ውሃ ሃብት ማዕከል ዳይሬክተር
• ክቡር ዶ/ር ጌታቸው ገብሩ፤ የኢትዮጵያ እንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት
• ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ም/ፕሬዝዳንቶችና የኮሌጅ ዲኖች ፤ቢሮ ሃላፊዎች፤ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የመጡ ተመራማሪዎችና አማካሪዎች
በአጠቃላይ ከ 100 በላይ እንግዶች በበዓሉ ላይ ታዳሚ ሆነዋል፡፡ የምረቃ በዓሉ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና በእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ሚኒስትር ዴዕታ የአበባ ሪባን በመቁረጥ የተበሰረ ሲሆን፤ ሁሉም እንግዶች ማዕከሉ በክልሉ መንግስት በጀት ድጋፍ በ 12 ሚሊዮን ብር ያስገጠመውን 30 ኩ/በሰዓት ፈጭቶና አደባልቆ ማውጣት የሚችል ዘመናዊ የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን፤ በአንዴ 76800 የለማ ዕንቁላል ማስታቀፍ የሚችል ዘመናዊ ኢንኩቤተር፤ አራት ብሎኮች እያንዳንዳቸው ከ 1800-2000 የተሻሻሉ የእንቁላል ጣይ እና የስጋ ዶሮ መሰረተ ርቢ መያዝ የሚችሉ ዘመናዊ ፋሲሊቲዎች የተጎበኙ ሲሆን፤በዝርያ መረጣ የተሻሻሉ ሁለት 7.2 እና 8 ሊትር ወተት በቀን መስጠት የሚችሉ የፎገራ ላሞች፤ ንጹህ የዋሸራ፤ፋርጣ እና የዋሸራና ፋርጣ ድቃይ (50%) በጎች ተጎብኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ ያወጣቸውና ያስተዋወቃቸው ቴክኖሎጂዎች የተቀመሩበት መጽሃፍ እና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፖስተሮች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

ማዕከሉ ላለፉት በርካታ ዓመታት በብዜት እና ምርምር ጉዞው ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት፤ያጋጠሙት ችግሮች፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት (2010-2015 ዓ.ም) ማዕከሉ ዘመናዊ የእንስሳት ምርምርና የስልጠና ማዕከል ለመገንባት ያሰበውን ፕሮጀክት ፕሮፖዛል የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር የሽዋስ ፈረደ አቅርበዋል፡፡ በሳይንቲስት ዶ/ር አዛገ ተገኘ ‘’My vision for Andassa: To be one of the best Livestock Research and Capacity Development Institute in Africa’’ በሚል ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን፤ የእርሳቸው ያልተጠበቀ አቀራረብ ብዙዎቹን ከማስገረም በዘለለ፤ ማዕከሉን ወደ ኢንስቲትዩትነት ለማሳደግ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በቂ የሆነ ወይይት ማድረግ እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በነበረው የፓናል ውይይት ዶ/ር ብሩ ይታፈሩ፤ ዶ/ር አዛገ ተገኝ፤ ዶ/ር ፍሬው ተገኝ፤ ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ እና ዶ/ር ገ/እግዚያብሄር ገ/ዮሃንስ ፓናሊስቶች ሆነው የተሰየሙ ሲሆን፤ ማዕከሉ ባቀረበው የፓናል ውይይት መነሻ ሃሳብ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡ ማሽነሪዎቹ ከውጭ አገር ተገዝተው እስኪተከሉ ድረስ እገዛ ላደረጉ የመንግስት መ/ቤቶች በእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴዕታ በክብርት ዶ/ር ምስራቅ መኮነን እና በአብክመ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ አባተ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም ዶ/ር ምስራቅ መኮነን በመዝጊያ ንግግራቸው ማዕከሉ እያደረገ ያለውን ጥረት አበረታትተው ማዕከሉ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታትና ቀጣይ እቅዶቹን በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲያደርግ የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል በመግባት የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል፡፡

በሁለተኛው ቀን (ሃምሌ 30/2009ዓ.ም) ማዕከሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ደረጃ የኢትዮጵያ እንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር (25th ESAP Silver Jubilee): የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጌታቸው ገብሩ እና የማህበሩ መስራች ዶ/ር አዛገ ተገኘ እና ፕ/ር አዱኛ ቶሌራ እንዲሁም ሌሎች ከተለያዩ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ባለሙዎች በተገኙበት፤ Enhancing Livestock Research, Education and Extension for Sustainable Economic Development in Amhara Region በሚል መርህ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ በዕለቱ ማዕከሉ የፎገራ ከብቶችን እና የዋሸራ በግ ዝርያዎችን ለማሻሻል የሰራቸውን ስራዎች፤ የምርምር ማዕከሉ የእንስሳት ዝርያዎቹን ማዕከሉ ለምን መጠበቅና ማሻሻል አስፈለገው በሚል አርዕስት የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርቧል፡፡ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በእንስሳት ምርምር ዘርፍ ለክልሉ እንሰሳት ሃብት እድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ በ ዶ/ር ሊቃውንት ይኸይስ፤ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የግብርና ሳይንስ ትምህርት ለግብርናው ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከዩኒቨርስቲው በ ዶ/ር ፍሬው ተገኝ ቀርቧል፡፡ በዕለቱ የተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ ጉዳዮች የተስተናገዱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ እንስሳት ሳይንስ ባለሙያዎች ማህበር 25ኛ ዓመት ምስረታን የሚያሳይ የኬክ ቆረሳ ስነ-ስርዓት በማካሄድ መጠናቀቁን የኢንስቲትዩቱ የህዝብ  ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ካስኬፕ ፕሮጀክት እና የክልሉ እንስሳት ሃብት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዝግጅቱን ስፖንሰር ስላደረጉ ኢንስቲትዩቱ ያለውን ከፍተኛ አድናቆት እየገለጸ ዝግጅቱ አምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ የአንዳሳ እንስሳት ምርምር ማዕከልና የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች ኢንስትትዩቱ ምስጋና ያቀርባል፡፡

 

l1

l2

 1. l3

 

 

 

Last Updated ( Monday, 18 September 2017 06:01 )
 
 • «
 •  Start 
 •  Prev 
 •  1 
 •  2 
 •  3 
 •  4 
 •  5 
 •  6 
 •  7 
 •  8 
 •  9 
 •  10 
 •  Next 
 •  End 
 • »
Page 1 of 21
You are here: Home